በአማራ ክልል ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየገባ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ለ2016/17 ምርት ዘመን የሚያገለግል ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሣህሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፥ በክልሉ ለ2016/17 ምርት ዘመን የሚያገለግል ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል።
ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ የመጀመሪያ ዙር ወደ ክልሉ ተጓጉዞ በኮምቦልቻ ከተማ መራገፍ መጀመሩን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት በተከሰተ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በግብርና ስራ ላይ ጫና በማሳደር በአርሶ አደሩ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን አስታውሰዋል።
ዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ፈጥኖ ከወዲሁ መጀመሩን አስታውቀው÷ የአፈር ማዳበሪያው ለታሰበው የሰብል ልማት ስራ ጥቅም ላይ እንዲውል በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
በክልሉ በ2015/16 ምርት ዘመን መኸር ወቅት የለማ ሰብል አሁን ላይ እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽና በምርት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል አርሶ አደሩ በፍጥነት የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።
በክልሉ በመኸር በወቅት ከ5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ዘር መሸፈኑንና እስካሁን በ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የምርት ስብሰባ ሂደቱ ከሰው ጉልበት በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲከናወን የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን አሁን ላይ እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ሌሎች ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎችን ማልማት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ በ2015/16 መኽር ወቅት በሰብል ከለማው መሬት ከ160 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የቢሮ ሃላፊው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡