Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች 850 ሚሊየን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት የመጀሪያ ሩብ በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ አንቀሳቃሾች 850 ሚሊየን ብር የገበያ ትስስር በመፍጠር የማጠናከር ስራ መከናወኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ፍቅረማርያም የኔአባት÷ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የሚገጥማቸውን የገበያ ትስስር ለማቃለል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር መታቀዱን ጠቅሰው÷ ከዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተደረገው ጥረት ከ850 ሚሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር የማጠናከር ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የገበያ ትስስሩ የተፈጠረው በተለያየ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ 12 ሺህ 600 አንቀሳቃሾች እንደሆነ አስታውቀዋል።

ትስስሩ የተፈጠረው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች በሚፈፅሟቸው ግዥዎችና ከኩባንያዎች ጋር በማገናኘት ነው ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ለ38 ሺህ ኢንተር ፕራይዞች 6 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.