በጋምቤላ ክልል የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ይፋ የተደረገውን የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ወደ ተግባር በመቀየር የአርሶ እና የከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ በትኩረት እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ግብርናን ለማዘመን የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ÷በክልሉ ለግብርና ልማት ሊውል የሚችለውን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በመለወጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በክልሉ ያለው ሀብት ለምቶ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷የፍኖተ ካርታው አካል የሆነው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን በሚደረገው ርብርብ አመራሩና ህዝቡ በተለይም የዘርፉ ተዋንያን የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል ÷የግብርናውን ዘርፍ ምርታማና ተወዳዳሪ በማድረግ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግ የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡