በሳይበር ምህዳሩ ላይ አቅሙን ያልገነባ ሀገር የሳይበር ደህንነቱን ማስጠበቅ እንደማይችል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለንበት የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በሳይበር ምህዳሩ ላይ ሁለንተናዊ አቅሙን ያልገነባ ሀገር የሳይበር ደህንነቱንና ሉዓላዊነቱን ማስጠበቅ እንደማይችል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ገለጸ፡፡
ኢመደአ በኢትዮጵያ ከማልታ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሳይበር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ÷ የሳይበር ምህዳር አንድ ተጨማሪ የዲፕሎማሲው የመንቀሳቀሻ ምህዳር በመሆኑ የሳይበር ዲፕሎማሲ አቅም መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በሳይበር ምህዳሩ ላይ ሁለንተናዊ አቅሙን ያልገነባ ሀገር የሳይበር ደህንነቱን እና ሉዓላዊነቱን ማስጠበቅ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ሀገራት በዓለም ዓቀፍ መድረክ ብሄራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅም ሆነ በተደራጀ እና በተሟላ መልኩ ድምጻቸውን ማሰማት እንደማይችሉ አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣው የሳይበር ዲፕሎማሲ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ እየቀየረ ከመምጣት ባሻገር ለሀገራት ልዩ ጥቅምና ስጋት መደቀኑን አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም በሳይበር ዲፕሎማሲ ላይ አሁናዊ እውቀት መለዋወጥ እና የሳይበር ዲፕሎማሲ ጥቅምን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መገለጹን፤ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡