በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የአገልግሎት መሟላት የቀጠናውን አቅም እንደሚያሳድግ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መሟላት የቀጠናውን አቅም እንደሚያሳድግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ፈርመውታል፡፡
አቶ አክሊሉ ታደሰ በወቅቱ እንደጠቆሙት÷ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት አንዱ ነው።
የዚህ አገልግሎት በነፃ ንግድ ቀጠናው መቀላጠፍ ቀጠናው ያለውን አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድግም ተናግረዋል፡፡
የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተቋማቸው በነፃ ንግድ ቀጠናው አስፈላጊውን አገልግሎት ለመጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኮርፖሬሽኑ ጋር ሀገራዊ ፋይዳው ጉልህ የሆነውን ነፃ ንግድ ቀጠና አገልግሎት ለማቀላጠፍ በቅንጅት ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳውቀዋል።
ስምምነቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና አስፈላጊውንና ዘርፈ ብዙ የሎጀስቲክስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የሚኖሩ አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች እንዲሁም በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚገኙ ባለሀብቶች የሚያስፈልጓቸውን የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች በተመደቡ ሰራተኞችና ኃላፊዎች በነፃ ንግድ ቀጠናው እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተገልጿል።
ስምምነቱ ቢሮክራሲን በማስቀረት፣ ጊዜን በመቆጠብና ከዚህ በፊት የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን የገቢ ወጪ ንግድና አገልግሎትን በማሳለጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡