በአማራ ክልል ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያስቀጥሉ ድጋፍ ይደረጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለሃብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ ልዑክ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት÷ በክልሉ እየተሻሻለ የመጣው የሰላም ሁኔታ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ መነቃቃትን እየፈጠረ መሆኑን በመግለጽ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን አቶ አብዱ ገልጸዋል።
በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርቶች የሚመጋገቡ ፋብሪካዎችን በማብዛት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ክልሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
ባለሃብቶችን በማበረታታት በችግር ጊዜም ችግርን ተቋቁመው ለኢትዮጵያና ለህዝብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በጉብኝቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እንዲሁም የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድአሚን የሱፍ ተገኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ የታየው አንዱ የክር ፋብሪካ ከውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተዛወረ በመሆኑ እሴት ጨምረው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡