Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር አለብን – አቶ ታዬ ደንደአ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት በመፍጠር በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናችንን ልንጫወት ይገባናል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።

የሰመራ፣ የወሎ፣ ወልዲያ እና የራያ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ያሰናዱት የምሁራን መድረክ ”ለሀገራዊ ማንነትና እሴት ግንባታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በውይይቱ መክፈቻ ላይ፥ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አረዳድ ከመያዝ ባለፈ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባናል ብለዋል።

የአንዳችን ሕመም ለሌላችን ሕመም፤ የአንዱ ደስታ ለሌላውም የሚያስደስት ሊሆን ይገባል በማለት ገልጸው፥ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ጉዳዮችን በማጎልበት ጠንክረው እንዲሰሩ ማስገንዘባቸውም ነው የተገለጸው።

ዩኒቨርሲቲዎች የኋላ ታሪክን ያጠኑ፣ የሚፈለገውን የለዩ፣ የወደፊት ራዕይን የተለሙ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸውም፥ በሥነ ምግባርና በጋራ እሴቶች ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ጊዜና ሃብት ለአዕምሮ ግንባታ መዋል እንዳለበት ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የዩኒቨርሲቲዎቹ ምሁራን ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማጥናት ጠቃሚና አመላካች ሀሳቦችን ሊያፈልቁ ይገባልም ነው ያሉት።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲዎች በሀገር ግንባታ የተሰጠንን ዓላማና ተልዕኮ ለማሳካት ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ምሁራን በጥናት፣ በምርምርና በትምህርት ዘርፎች ለሀገር ግንባታ ድርሻችን መወጣት አለብን ሲሉም ነው የተናገሩት።

በውይይቱ ላይ የአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች አመራር አባላት ሌሎች እንግዶች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.