ከተማ አስተዳደሮች የባለሀብቱን ፍላጎት የሚያሟላ አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ አሕመዲን (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በደብረ ብርሀን ከተማ በማምረትና ግንባታ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)÷ በክልሉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የመሰረት ልማትና የማስፋፊያ መሬት ጥያቄዎች አሏቸው ብለዋል፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች በፍጥነት በመፍታት ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉም ገልጸዋል።
ሰላም ለኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የክልሉ መንግስት አሁን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ከተማ አስተዳደሮች የባለሀብቱን ፍላጎት የሚያሟላ አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል ያሉት ሀላፊው÷ የተንዛዛ ቢሮክራሲን ማስቀረት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአላዩ ገረመው