ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን ለግብርናው ምርታማነት በመጠቀም ምሳሌ ናት- ተመድ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ልማትን ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በመጠቀም ኢትዮጵያ ምሳሌ የምትሆን ሀገር ናት ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ተናገሩ።
20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባዔ ኦስትሪያ ቪዬና እየተካሄደ ነው፡፡
የድርጅቱ ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር በጉባዔው ላይ እንደገለጹት÷ ድርጅቱ ሀገራት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለዘላቂ ልማትና ብልጽግና እንዲጠቀሙት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን ይቀርጻል።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማቱን ለግብርናው ዘርፍ መነቃቃትና ምርታማነት በማዋል በምሳሌነት እንደምትጠቀስም ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለዘርፉ ምርታማነት በመጠቀም በተለይ በስንዴ፣ ሩዝ እንዲሁም በቆሎን በመሳሰሉት የሰብል ምርቶች አመርቂ ውጤት እንዳስመዘገበች ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በስንዴ ልማቱ የተመዘገበው ውጤት ሀገሪቱን የስንዴ ምርት ከውጭ ከማስገባት ወደ ውጭ ለመላክ እንዳስቻላት ጠቅሰው÷ ይህም ምሳሌ እንደሚያደርጋት አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ልማቱን ለግብርናው በመጠቀም የተገኘው ውጤት ከሰብል ባሻገር በቡና ምርት ላይ ታይቷ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህም የቡናው ዘርፍ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በገንዘብ ከሚገኘው ገቢ ባሻገር በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት በንግግራቸው።
ሀገራት የኢንዱስትሪ ልማትን ለግብርናው ምርትና ምርታማነት መጨመር እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ከኢትዮጵያ ልምድ እንዲቀስሙም አስገንዝበዋል።