ጅቡቲ ከደረሰው 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከ1 ሚሊየን በላይ ወደ ሀገር ተጓጉዟል – ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅቡቲ ከደረሰው 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር መጓጓዙን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፤ ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ቢሆንም 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የመግዛት አቅም ብቻ እንዳለ ገልጸዋል።
የ930 ሚሊዮን ዶላር ወይም 71 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማዳበሪያ ግዢ መመደቡን ጠቅሰው፤ ያም ሆኖ ግን ከሚያስፈልገው የማዳበሪያ ግብዓት ፍላጎት አንጻር ምንም አይነት እጥረት እንዳይፈጠር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
8 ነጥብ2 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ እና 11 ነጥብ19 ሚሊየን ኩንታሉ ኤን ፒ ኤስ የማዳበሪያ አይነት እንደሚገዛ ገልጸው፤ እስካሁን የ11 ነጥብ 19 ሚሊየን ኩንታል ኤን ፒ ኤስ እና የ 3 ነጥብ 56 ሚሊየን ኵንታል ዩሪያ ማዳበሪያ በድምሩ 14 ነጥብ 79 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።
ቀሪውን ለመግዛትም ዋጋ የሚረጋጋበት ምቹ ወቅት እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል።
የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ ቀድሞ መጀመሩን ጠቅሰው፤ እስከ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጅቡቲ ከደረሰው 2ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ ከ1ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።
በተመሳሳይ ከህዳር 21 እስከ ታሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስም ኤን.ፒ.ኤስ ቦሮን የጫኑ 3 መርከቦች ጅቡቲ ወደብ የሚደርሱ ይሆናል ተብሏል።
በይስማው አደራው