Fana: At a Speed of Life!

ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ወጥነት ያለው አሰራርና የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ወጥነት ያለው የአሰራር መስፈርትና የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት-ፋኦ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚከናወንም ተገልጿል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ጥናት፣ ዲዛይንና ጥገና ረገድ አሁንም ተግዳሮቶች አሉ።

ለአብነትም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ አቅም ውስንነት፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ የጥራት እንዲሁም በተያዘላቸው ጊዜ ገደብና በጀት አለመጠናቀቅ ከሚስተዋሉ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጥ አሰራር እና መመሪያ ባለመኖሩ 75 በመቶ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በዲዛይን ጥራት ችግር እንደሚጓተቱ ጠቁመዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና የተፈጥሮ ሀብት ያገናዘበ የመስኖ ልማትን ለመደገፍ ወጥነት ያለው የአሰራር መስፈርት፣ መመሪያና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

ይህን እውን የሚያደርግና በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ ይፋ መደረጉን ጠቁመዋል።

የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት-ፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ በበኩላቸው÷ድርጅቱ የኢትዮጵያን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ በአቅም ግንባታ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

የመስኖ ልማት የአሰራረ መስፈርትና መመሪያን ለማዘጋጀት ይፋ የሆነው ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን ድጋፉን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)÷ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.