Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንሰራለን – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ሶዶ ማዕከል ከሚገኙ የክልል ቢሮ አመራር አባላትና ሰራተኞች ጋር በቀጣይ የሥራ ሂደትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ተወያይተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ በሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ሰራተኛው የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አገልግሎት በመስጠት የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አዳጊ ፍላጎቶች የሚወልዷቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ አገልግሎቶችን በማዘመንና በወቅቱ በመመለስ ተምሳሌት የሚሆን ክልል ለመፍጠር መትጋት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

“እቅዶቻችንን ወደ መሬት በማውረድ ህዝባችንን በልማት ለመካስ ጥረቱ ሊጠናከር ይገባል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ ህዝብን በትጋት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.