Fana: At a Speed of Life!

የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች ወደ ሕብረተሰቡ ሊቀላቀሉ ነው

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 30 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች በቅርቡ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ ሊቀላቀሉ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ኮማንድ ፖስት የጎንደር ቀጣና ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዋኘው አለሜ ገለጹ።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠዳ ወረዳ የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ታጣቂዎች መንግሥት ላደረገላቸው የሰላም ጥሪ አመስግነው ሕዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙትን በመጎብኘት ከኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪዎች ጋር መወያየታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሰሜን ምዕራብ ኮማንድ ፖስት የጎንደር ቀጣና ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዋኘው አለሜ፥ በተለያዩ ቅስቀሳዎች በመደናገር ወደ ጫካ የገቡ ታጣቂዎችን ኮማንድ ፖስቱ መስፈርቶችን በማውጣት በወዶገብነት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም በአማራ ክልል ጎንደር ቀጣና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች በቅርቡ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉ አረጋግጠዋል።

በጎንደር ቀጣና እስካሁን 528 ታጣቂዎች ጥሪውን መቀበላቸውን ጠቅሰው፥ ከእነዚህ መካከልም 234 የሚሆኑት ከእነመሳሪያቸው የገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች እና ወረዳዎች የወንጀል ሪከርድ እንደሌላቸው ተረጋግጦና የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው አካባቢያቸውን የሰላም ዘብ በመሆን እንዲጠብቁ ይደረጋል ብለዋል።
ከ528ቱ ታጣቂዎች መካከልም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 119 የሚሆኑት የተሃድሶ ሥልጠና መውሰድ መጀመራቸውን ጠቁመው፥ ቀሪዎቹም በቅርቡ ሥልጠና እንዲጀምሩ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠዳ ወረዳ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ታጣቂዎችም መንግሥት ላደረገላቸው የሰላም ጥሪ አመስግነው ሕዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በአግባቡ ተከታትለው በማጠናቀቅ በአካባቢያቸው የሰላም አምባሳደር እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላቱ አብርሃም በርታ (ዶ/ር)፥ ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመሰልጠን ሕብረተሰቡን ለመቀላቀል መዘጋጀታቸውን በውይይቱ አረጋግጠናል ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋርም ውይይት አድርጓል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.