በሐረሪ ክልል ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ከኢትዮዽያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ በጁገልና ገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ በተዘጋጀው ጥናት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ÷ በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሰራል ብለዋል፡፡
የቀረበው ጥናት ወደ ትግበራ ሲገባ ቅርሶችን ለመንከባከብ ለመጠበቅና ለህብረተሰቡና ለክልሉ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ስርአት ለመገንባት የሚያስችል አቅም በመፍጠር ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገርም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ የተጀመረውን ኢኒሼቲቭ በጥናት በተደገፈ መልኩ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሃይሉ በበኩላቸው÷ ባለስልጣኑ ክልሉ ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ የሚያደርገውን ተግባር መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።