የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የታሪፍ ማሻሻያ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የአዲስ አበባ- አዳማ፣ የድሬዳዋ ዳዋሌ እና የሞጆ-ባቱ የክፍያ መንገድ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ኢንተርፕራይዙ ሁለት ጊዜ ብቻ የታሪፍ ማሻሻያ እንዳደረገ አስታውሶ፤ የመጀመሪያው የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ በመጋቢት 2011 ዓ.ም በአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ ላይ የተተገበረ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ለአራት አመታት የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ ሳይደረግ ቆይቶ በሕዳር 2015 ዓ.ም ውጤታማ የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ ተተግብሮ እንደነበር ገልጿል፡፡
የስራ ማስኬጃና መደበኛ ጥገና ወጪዎች የዋጋ ግሽበትን በመቋቋም ተቋማዊ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ በማሰብ የታሪፍ ማሻሻያውን ማድረግ እንዳስፈለገም አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ለወቅታዊ ጥገና መጠባበቂያ ፈንድ ዓመታዊ ተቀማጭን በማረጋገጥ የክፍያ መንገዶችን የአገልግሎት ደረጃ ለማስጠበቅ የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን አብራርቷል።
ትርፍ በማስመዝገብ የመንግስት የትርፍ ድርሻ አስተዋጽዖን ለመወጣት የሚያበቃ የፋይናንስ አቋምን ለማረጋገጥ ዓመታዊ የክፍያ መንገዶች የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ተመን መወሰን አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
የአዲስ-አዳማና የሞጆ-ባቱ የፍጥነት መንገዶች የአገልግሎት ደረጃቸው በፍጥነት መንገድ ደረጃ ያሉና ተመጋጋቢ የክፍያ መንገዶች በመሆናቸው በአንድ ዓይነት የታሪፍ ተመን ይተዳደራሉም ነው የተባለው፡፡
በዚህም ለአዲስ-አዳማ እና የሞጆ-ባቱ የፍጥነት መንገዶች በተመሳሳይ 31 በመቶ ሲሆን÷ ለድሬደዋ ዳዋሌ የክፍያ መንገድ 42 በመቶ የታሪፍ ዕድገት እንዲኖረው መደረጉን የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ መረጃ ያመላክታል፡፡
በድሬዳዋ-ዳዋሌ የክፍያ መንገድ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ይከፍሉ የነበረው ታሪፍ ብር 10 ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ታይቶ ማህበረሰቡ ለተጋነነ ትራንስፖርት ወጪ ጫና እንዳይዳረግ የአገልግሎት ክፍያ ታሪፉ በልዩ ሁኔታ ባለበት ይቀጥላል ተብሏል፡፡