የቴክኒክና ሙያ አሰላሳይና ሐሳብ አመንጪዎች ቡድን ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቴክኒክና ሙያ አሰላሳይና ሐሳብ አመንጪዎች ቡድን /ቲንክ ታንክ ግሩፕ/ በአዲስ አበባ በይፋ ተመስርቷል፡፡
የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በምሥረታው ላይ እንዳሉት፥ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣ በእውቀት፣ በጥናትና ምርምር መደገፍ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም አዳዲስ አሠራሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚፈልቁበትን አሠራርና አደረጃጀት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የተመሰረተው የቴክኒክና ሙያ አሰላሳይና ሐሳብ አመንጪዎች ቡድንም ጥሩ ጅምር መሆኑን ጠቅሰው፥ ሀገራዊ የልማት ተልዕኮን ለማሳካት የላቀ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም የሪፎርም እሳቤዎችን ውጤታማ ለማድረግና ተወዳዳሪ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የማይተካ ሚና አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበከሉላቸው፥ በዘርፉ አሰላሳይና ሐሳብ አመንጪዎች ቡድን መመስረቱ የሀገሪቱን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል፡፡
የቡድኑ መመስረት በፖሊሲ አተገባበር ሂደት ውስጥ የካበተ ሐሳብ በመስጠት፣ ልምዶችን በማካፈል፣ የውይይት ባህል እንዲዳብርና በዘርፉ ተዋንያን መካከል ተቀራርቦ ለመሥራት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡