Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ የእርቀ ሰላም መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከጋምቤላ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ያዘጋጁት የእርቀ ሰላም መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጅሉ፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚህ ወቅት÷ መርሐ ግብሩ ከቂም የፀዳ የይቅርታ ባህል የሰፈነበትን ማህበረሰብ ለመገንባት መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

ዘላቂ ሰላም የሰፈነበትና የክልሉ ህዝብ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ያለውን አቅም በማቀናጀት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰላም ካለ ሰው በሰላም ገብቶ ይወጣል፤የዘራውንም ያጭዳል፤ ያጨደውንም ወቅቶ ወደ ገበያ ያቀርባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ሁሉም የአካባቢውን ብሎም የክልሉን ሰላም በመጠበቅ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቲያንግ ኡቻን በበኩላቸው÷ ተቀራርቦ መነጋገር ይበልጥ የመተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥርና ለሰላምና አብሮ ለመኖርም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

ችግሮችን በውይይት እንዲሁም በእርቅና ይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አሁን የሚፈፀመው የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ካለፈው ጥፋታችን ታርመን በእርቅና ይቅርታ ዘግተን በወንድማማችነት መንፈስ ፊታችንን ወደ ልማት ማዞር አለብን ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በሰላም ሚኒስትር የፌደራሊዝምና መንግስታት ግንኙነት መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ሀይሌ÷ ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

በውይይቱ የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ችግሮቻችንን በውይይት በመፍታት ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ እንድገትና ልማት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.