Fana: At a Speed of Life!

በሸገር ከተማ መኖሪያ ቤቶችን ሰብረው ገብተዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ በሙስና ወንጀል በምርመራ የታሸጉ መኖሪያ ቤቶችን ሰብረው ገብተዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክ/ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ነው።

የኮዬ ፈጬ ክ/ከተማ ምድብ ዐቃቤ ሕግ ዘጠኝ መዝገቦችን በማደራጀት ገላሞ ዋቤ ሀጂን ጨምሮ አጠቃላይ 13 ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቷል።

በክስ ዝርዝሩ ላይ በሸገር ከተማ በኮዬ ፈጬ ክ/ከተማ ሀጫሉ መንደር እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ከተሰሩ መኖሪያ ቤቶች መካከል በሙስና ወንጀል ድርጊት ለምርመራ የታሸጉ 13 ቤቶችን ተከሳሾቹ ሰብረው መግባታቸው ተጠቅሶ የወንጀል ህግ አንቀጽ 439 ሀ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በዚህ መልኩ በዘጠኝ መዝገቦች በዐቃቤ ሕግ ተደራጅተው የቀረቡ ክሶችን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ በክሱ ላይ የግራ ቀኝ ክርክር ለማድረግ ለታኅሣስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚሁ መኖሪያ ቤትን ከሶማሌ ክልል ተፈናቃይ ነን በማለት በማጭበርበር በተፈናቃዮች ስም ያለአግባብ በመውሰድ የድጎማ ገንዘብ በመቀበል ጭምር በተፈጸመ የሙስና ድርጊት ከ8 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉና በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ 50 ግለሰቦች ላይ የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ 3 የሙስና ወንጀል ክሶችን አቅርቦ በክልሉ ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሂደት ላይ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.