Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ አዳዲስና ነባር የገበያ ማዕከሎች ለ3ኛ ወገን ሊተላለፉ ነው ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህብረተሰቡን ዕርካታ በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል 12 አዳዲስና ነባር የገበያ ማዕከሎች ለ3ኛ ወገን ሊተላለፉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ ከሚተላለፉት ማዕከላት ውስጥ የለሚ ኩራ እና የኮልፌ የግብርና ገበያ እና የአቃቂ ቃሊቲ የሰብል ምርቶች መሸጫ ማዕከላት እንዲሁም የላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ማስፋፊያ ማዕከል ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የሸጎሌ የዳልጋ ከብቶች፣ የብርጭቆ የበግና ፍየል የቄራ የቁም እንስሳሳት ማዕከላት እና ተጨማሪ አምስት የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የገበያ ማዕከላቱን ለባለሃብቶች በጨረታ ለማስተላለፍ ሂደት ላይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሚቀጥለው ወር ወደ ስራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል፡፡

ባለሃብቶች የማስተዳደር ስራውን ሲረከቡ መንግስት ደግሞ የቁጥጥር ተግባሩን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

አምራቾች የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ሰውነት፤ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ምርቶችን በጥራትና በስፋት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ለ3ኛ ወገን ማስተላለፉ አንዳንድ የገበያ ማዕከላት ላይ የጽዳት፣ የጥበቃ እንዲሁም ተቋማቱን ከታለመላቸው ዓላማ ከመጠቀም አኳያ አልፎአልፎ የሚስተዋሉና ተያያዥ ችግሮችን ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.