ኢትዮ ቴሌኮም አራት አገልግሎቶችን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የላቀ የድምጽና የምስል ጥራት ያለው የስልክ ጥሪ እንዲኖር የሚያስችሉ አገልግሎቶችን በዛሬው ዕለት ለደንበኞቹ አስተዋውቋል፡፡
ይፋ የተደረጉት አገልግሎቶችም÷ የ “ቮልቲኢ አገልግሎት”፣ “ሪች ኮሙኒኬሽን አገልግሎት”፣ የ “መልቲሚዲያ መልዕክት አገልግሎት” እና “የድምፅ መልዕክት አገልግሎት” ናቸው፡፡
የ“ቮልቲኢ አገልግሎት” የ4ጂ ኔትወርክ በስፋት ተደራሽ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ደንበኞች የላቀ የድምጽና የምስል ጥራት ያለው የስልክ ጥሪ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
እንዲሁም “ሪች ኮሙኒኬሽን” የተሰኘ አገልግሎት÷ የግለሰብና የቢዝነስ ደንበኞች የመደበኛ የመልዕክት አገልግሎት ተጠቅመው መልዕክቶችን እንዲያጋሩ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሌላኛው ዛሬ ይፋ የተደረገው የ“መልቲሚዲያ መልዕክት አገልግሎት” ሲሆን÷ የቪድዮ እና የድምፅ መልዕክቶችን ያለገደብ በአንድ ጊዜ መላክ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
“የድምፅ መልዕክት አገልግሎት”÷ ደንበኞች ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ ደዋዩ የድምፅ መልዕክት እንዲያስቀምጥ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
በቤተልሔም መኳንንት