የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ለህዝብ በገባውን ቃል መሰረት እየሰራ እንደሆነ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለመረጠው ህዝብ በገባው ቃል መሰረት ከህዝቡ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የልማት ጥያቄዎችና የአገልግሎት አሰጣጥን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን የፓርቲው የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ገለጸ።
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሰሩ ስራዎችን “ሁለንተናዊ የብልፀግና ጉዞችን ጅምር ስኬቶች” በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሐርብ ቡኽ እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በልማትና በሰላም ህዝብ ተኮር የሆኑ ስራዎች ተከናውነዋል።
ለዚህም የህብረተሰቡ ሚና የላቀ እንደነበር ገልጸዋል።
የፓርቲው የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ለመረጠው ህዝብ በገባው ቃል መሰረት የመልካም አስተዳደር፣ የልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለህዝቡ የሚጠቅሙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ ተግዳሮቶች ለመፈተሽና ለማስተካከል አቅጣጫ መቀመጡንና ቅድሚያ ለህዝብ ተጠቃሚነት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በቀረበ ፅሁፍ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በምንያህል መለሰ