በተቋማችን ባካሄድነው የለውጥ ስራዎች የማድረግ አቅማችችንን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተቋማችን ባካሄድነው የለውጥ ስራዎች የማድረግ አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገናል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የቀጣናችን ስትራቴጂክ ሁኔታ ሀገራችን ላይ በሚኖረው ተጽዕኖ፤ ዓለም አቀፍ የሀይል አሰላለፍና የውጊያ ዐውድ አኳያ ኢትዮጵያ አቅሟን ባልተቋረጠ መልኩ እያሳደገችና እያዘመነች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም አየር ሀይልን፣ ባህር ሀይልን፣ ምድር ጦርን፣ የሳይበር ሀይልንና ሌሎችም አቅሞችን የማዘመን፣ የማጠናከርና የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተቋማችን ባካሄድነው የለውጥ ስራዎች ሁሉንም ሃይሎቻችንን በአደረጃጀት በስነ ልቦናና በትጥቅ ባልተቋረጠ ሁኔታ በማዘመን የማድረግ አቅማችችንን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በመስራት ትልቅ እምርታንም አምጥተንበታል ብለዋል።
አየር ሀይሉ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት እጅግ ደካማ አደረጃጀትና ቁመና እንደነበረው አስታውሰው፤ ይህንን የመቀየር ስራ በመስራት የማድረግ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
አየር ሃይልን በሁሉም መስክ ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር አየር ሃይልን አስተማማኝ የሀገር አለኝታ እንዲሆም መደረጉን ገልጸዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአየር ሀይሉ መዘመን ላደረጉት ሁለንተናዊ ድጋፍም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
እንዲሁም የአየር ሃይሉ ባልደረቦችና ሌሎች አጋሮችም ላደረጉት አስተዋጽኦ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምስጋና አቅርበዋል።