Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሜላተወርቅ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ይሠራል አሉ

አዲስ አበባ፣ ታኀሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብስባ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ከመንግሥት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

ወ/ሮ ሜላተወርቅም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ቦርዱን ለመምራት በሕዝብና በመንግሥት የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የቦርዱን ስኬቶች በማስጠበቅ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነትም ለመጨመር ከሌሎች አመራሮች ጋር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

ቦርዱ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ የሕዝብን ፍላጎት ከማርካት አኳያ የሚነሱ ክፍተቶችን መፍታት ቀዳሚ ሥራ እንደሚሆን አመልክተዋል።

በቦርዱ አሠራር ላይ ቅሬታ ያለው አካል በተዘጋጁ የጥቆማ መስጫዎች ወይም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀው÷ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም አረጋግጠዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.