Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር የአገራቱን የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቁ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ናት – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር የሁለቱ አገራትን የጋራ ጥቅምና ፍላጎት በሚያስጠብቁ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ናት ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮ-ሩስያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽንና ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ፎረሙን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሲሆን÷ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ የሁለቱ አገራት የሥራ ኃላፊዎችና ባለኃብቶች እየተሳተፉ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮ-ሩስያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ሰብሳቢ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ኢትዮጵያና ሩስያ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

ግንኙነቱን በንግድና በኢንቨስትመንት መስክም የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ለዚህም አገራቱ በጋራ ለመበልፀግ አስቻይ እምቅ አቅም ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

በአገራቱ መካከል የተፈረሙ ሥምምነቶች ትብብሩን የበለጠ ለማስፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውን በመግለጽ÷እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሩስያ የማዕድን ኃብት ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው÷ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ትብብር በብሪክስ ማዕቀፍም ለማጎልበት እንደምትፈልግ ገልፀዋል።

በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መጥቷል ያሉት ኃላፊው÷የንግድ ልውውጡም እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ሃገራቱ በትምህርት፣ በባህል፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በሥራ ቅጥር መስኮችም ግንኙነታቸውን የሚያጎለብቱ ትብብሮች መጀመራቸውን አንስተዋል።

የሩስያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ በሩስያ መንግሥት በኩል አስፈላጊ ጥረቶች እንደሚደረጉም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮ-ሩስያ የጋራ ፎረም ነገም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን÷የሁለቱ አገራት የቢዝነስ አንቀሳቃሾች የሚሳተፉበት የቢዝነስ ፎረም እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.