Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ መፍትሔ ላይ ለመድረስ በቁርጠኝነት ትቀጥላለች – ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታኅሥስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድና በፍትሐዊ ድርድር የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት ይዛ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እና በፍትሐዊ ድርድር የሶስቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት ይዛ እንደምትቀጥልም ሚኒስቴር በመግለጫው አረጋግጧል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

ከታህሣስ 7 እስከ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ሀገራቱ አራተኛውን ዙር የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ አካሀ ማካሄዳቸውን ገልጿል።

አራት ዙር ድርድር የተካሄደው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ የጋራ መግባባት መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው።

መሪዎቹ ለባለሙያዎች አቅጣጫ በመስጠት የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ አሞላልና ዓመታዊ ስራን አስመልክቶ የወጣውን ደንብና መመሪያ አጠናቅቆ ለማስቀጠል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እንዲደረግም ጥረዋል።

ይህ ለአራት ዙር የዘለቀው ድርድር ሶስቱ ሀገራት በመካከላቸው ያሉ ዋና ዋና ልዩነት ፈጣሪ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንዲያደርጉ ማገዙም እንደማይዘነጋ መግለጫው ጠቁሟል።

በእነዚህ አራት ዙሮች ኢትዮጵያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ልዩነቶችን ለመፍታትና የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጋለች።

ይሁን እንጂ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን ይዛ በመቀጠል ወደ ስምምነትና ትብብር የሚወስደውን መንገድ ዘግታለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ አሰራር መመሪያ እና ደንቦች ላይ የተደረገው ድርድር በሶስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር እንጂ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያን መብት ለመንጠቅ ያለመ አይደለም ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ ላይ በመመስረት የአሁንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ይፋ ማድረግ እንደምትፈልግ አስታውቋል።

በፈረንጆቹ 2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ለዚህ ድርድር መሰረት ነው ያለው መግለጫው ከዚህም በላይ በፈረንጆቹ ከ2020 ጀምሮ ጉዳዩን የያዘው የአፍሪካ ኅብረት ሦስቱ አገሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ መፍትሔ ሀሳብ እንዲመጡ ዕድል የሚፈጥርበትን መድረክ ማመቻቸቱን አስታውሷል።

አራተኛው ዙር ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ህብረት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን የሚጻረር መግለጫ ግብጽ ማውጣቷን የጠቀሰው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበባትን የተሳሳተ መረጃም አትቀበለውም ብሏል።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እና በፍትሐዊ ድርድር የሶስቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት ይዛ እንደምትቀጥልም ሚኒስቴር በመግለጫው አረጋግጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.