Fana: At a Speed of Life!

በራሱ አቅም ሄሊኮፕተር የሰራው ኢትዮጵያዊ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዕበ ለገሰ ይባላል፣ ትውልድ እና እድገቱም በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሴ አካባቢ ነው፡፡

ዕበ በህጻንነቱ በሰማይ ላይ የሚበሩ ሄሊኮፕተሮችን ሲመለከት በሁኔታው ይደነቅ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ሄሊኮፕተር የመስራት ዝንባሌ አደረበት።

በትምህርት ቆይታውም በትምህርት ቤቶች በሚገኙ የፈጠራ ማዕከላት በመሳተፍ ለኤሌክትሮኒክስ ስራዎች የተለየ ትኩረት ማድረጉን ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ገልጿል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ ሥራ ላይ ያለውን ልምድ በማዳበርም ቀስ በቀስ የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጥገና ሥራ፣ የወርቅ ማውጫ ማሽን ሥራ እና ሌሎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት እንደጀመረ ያስረዳል፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎንም የልጅነት መደነቁ፣ ህልሙና ፍላጎቱ የነበረውን ሄሊኮፕተር ለመስራት ወስኖ የተግባር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ።

አንድን ሥራ ለመጀመር በጥንቃቄ ማሰብ እና መወሰን ያስፈልጋል የሚለው ዕበ÷ ከጀመሩ በኋላም የራስን አቅም በማዘመን ሥራውን እስከ ስኬት ድረስ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ይናገራል፡፡

በዚህ እሳቤውም ሄሊኮፕተሩን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካባቢ ከሚገኙ ቁሶች ለመስራት መሞከሩን እና በዚህም ልምድ ማግኘቱን አንስቷል፡፡

በመቀጠልም ሰው ተሸክሞ መብረር የሚችል ሄሊኮፕተር መስራት እንደሚቻል በማሰብ በአዲስ መንፈስ ሥራ መጀመሩን ነው የሚገልጸው፡፡

ለዚህም ለሄሊኮፕተር መስሪያ እንደ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ሞተር፣ አልሙኒየም እና ሌሎች መሳሪያዎችን ማሟላት ይጀምራል፡፡

በዚህ መልኩ የሰራው ሄሊኮፕተርም ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ አለመሳካቱን ጠቁሞ፤ ተስፋ ሳይቆርጥ በቀጣይ አሻሽሎ ለመስራት ወስኖ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የተሻለ ግብዓት በመጠቀም መብረር የሚችል ሄሊኮፕተር መስራት መቻሉን ተናግሯል፡፡

ለ6ኛ ጊዜ የሰራው ይህ ሄሊኮፕተርም ለ3 ደቂቃ ያህል በሰማይ ላይ መብረር እንደሚችል ነው የሚገልጸው፡፡

በዚህም በቅርቡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባዘጋጀው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ላይ 1ኛ በመውጣት መሸለሙን ተናግሯል፡፡

ሄሊኮፕተሩ ከሞተር ውጪ በሀገር ውስጥ ግብዓቶች እንደተሰራ የሚናገረው ዕበ÷ ለእሳት አደጋ፣ ለአንበጣ መንጋ መከላከያ፣ ለሽርሽር፣ ለአንቡላንስ እና ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

በቀጣይ ሄሊኮፕተሩን አሸሽሎ ለመስራትና ችግር ፈቺ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ አየር ሃይል ድጋፍ እንደሚያደርግለት ቃል መግባቱንም ጠቅሷል፡፡

ወደ ፊት ሥራውን በፕሮጀክት መልኩ ይበልጥ ለማስፋፋት እና ገበያ ላይ ለማዋልም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.