የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበው ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ መወያየቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስት ለሕዝብ ጥቅም በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ሲባል የመሬት ይዞታ እንዲለቁ ለሚደረጉ ባለይዞታዎች ተገቢና ተመጣጣኝ ምትክ ይዞታ፣ ካሣ መስጠትና ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል ግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸውን መሠረታዊ መርሆች ለመደንገግ፣ ካሣን የመተመን፣ የመክፈል እንዲሁም ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ሥልጣንና ኃላፊነት የተጣለባቸውን አካላትና ግዴታዎቻቸውን ግልጽ ማድረግ በማስፈለጉ በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 1161/2011 የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡
በልዩ ልዩ ዘርፎች የላቀ ተግባር ለፈጸሙ ዜጎች እውቅና መስጠት በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ለሀገር ለሚያበረክቱት የላቀ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ባለውለታ አድርጋ እንደምታከብራቸው እውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም የእነርሱን አርአያነት እንዲከተሉ የሚያበረታታ፣ የስራ ፈጠራ እንዲስፋፋ፣ ሁለንተናዊ እና ቀጣይነት ያለው ብልጽግና እንዲረጋገጥ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የሜዳይ፣ የኒሻንና የሽልማት አሰጣጥ ስርዓት መተግበር የሚያስችል፣ ለአተገባበሩም ሕጋዊ ሥርዓት የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላትን፣ የዕረፍት ቀናትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡
የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀናት ለዜጎች ሥነ-ምግባርና ስነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦዋችው ከፍተኛ በመሆኑ ሕጋዊ እውቅና መስጠት እና በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩ ማድረግ የሚገባ በመሆኑ፤ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው ሊከበሩ የሚገባ በመሆኑ፤ የዜጎችን የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነትና መተሳሰብ የሚያጎለብቱ እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል እንዲጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው በአምራች ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትና መዋቅራዊ ሽግግር መሳለጥ የላቀ ሚናውን እንዲወጣ፤ ለውጪ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ መደላድል የሚሆን የፖሊሲ ማእቀፍ ሚያስፈልግ በመሆኑ፤ የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማበረታታት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በአካባቢና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ክብካቤ መርሆች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስር ለማሳደግ የሚያስችል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡