Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አማራጮች አሏት – የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 10 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ጋር በኢትዮጵያና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የጸጥታና የፖለቲካ ጉዳዮች የምክር ቤቱ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የጸጥታ ችግር፣ የፌዴራል ስርዓት፣ የባህር በር ጥያቄ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲሁም የሴቶች መብት አጠባበቅን በሚመለከት ማብራሪያ ጠይቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)÷ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ስለመገባቱም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያነሳች ያለው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህጎች መሰረት በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሏት በርካታ አማራጮች እንዳሉ በመጥቀስም፥ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሌሎች ሉዓላዊ ሀገራት ጣልቃ መግባትን እንደማይደግፍ ገልጸዋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ቢያገኝ የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ምክር ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.