በፍራሽ ውስጥ ተደብቆ ወደ ጋምቤላ ከተማ የገባ 80 ኪ/ግራም አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍራሽ ውስጥ በመደበቅ ከመሀል ሀገር ወደ ጋምቤላ ከተማ የገባ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ መያዙን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡሞድ ኡሞድ እንደገለጹት÷ ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት ከሰዓት 11 ሰዓት አካባቢ ነው።
በዕለቱ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በጋምቤላ ከተማ 01 ቀበሌ በ10 ፍራሽ ውስጥ በስውር ተሰፍቶ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝን 98 ጥቅል አደንዛዥ ዕፅ መያዙን አስታውቀዋል።
ከአደንዛዥ እፁ ጋር ተያይዞ አንድ ተጠርጣሪ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከመሀል ሀገር ጭኖ የመጣውን አሽከርካሪ እና ግለሰብ ለመያዝ ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ እንደሚገኘ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰብ ጤና ጠንቅ የሆነው ማንኛውንም ዓይነት ተክል ለምቶ ከተገኘ ህብረተሰቡ አጋልጦ ለህግ አስከባሪዎች እንዲጠቁም መልዕክታቸወን አስተላልፈዋል።