Fana: At a Speed of Life!

የምክክር ኮሚሽኑ በእስያ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በእስያ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ ውይይት አደረገ፡፡

በመድረኩ ላይ በእስያ፣ አውስትራሊያና ኒውዚላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ተሳትፎና ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ድጋፎች ውይይት ተደርጓል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙ የኮሚሽኑ አባላት ኮሚሽኑንና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በተመለከተ የተለያዩ ገለፃዎችና ማብራሪያዎች መስጠታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም ስለሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ፅንሰ-ሀሳብ፣ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ስላለው ፋይዳ፣ በኮሚሽኑ ስለተከናወኑ አንኳር ተግባራት እና ኮሚሽኑ ስለሚገዛባቸው የህግ ማዕቀፎች መግለጫዎችን አቅርበዋል፡፡

ገለፃውን ተከትሎ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ፥ ኮሚሽኑ በእሲያ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር ስለሚሰራባቸው መንገዶች የተለያዩ ምክረ-ሀሳቦች መቅረባቸውም ነው የተነሳው፡፡

በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአሰራር ሂደቱ ላይ ሊያስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተነስተው አቅጣጫ ጠቋሚ የሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.