አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው ታኅሣስ ወር አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንዳሉት፥ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ሲዳማ ክልሎች ይገነባሉ።
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም ከ19 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በማልማት ከ38 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።
ፕሮጀክቶቹ የፈንታሌ መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ የሎጊያ ሎት 1 ግድብና ተያያዥ ሥራዎች፣ ሽንሌ የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማት ፕሮጀክት እና ጊዳቦ ሎት 2 የቀኝ ክንፍ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ2 እስከ 3 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመሳፍንት እያዩ