Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት የ1 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ሥምምት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ታኀሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የ1 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ሥምምት ተፈራርመዋል፡፡

የድጋፍ ስምምነቱን የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

የድጋፍ ሥምምነቱ የፕሪቶሪያውን የሰላም ሥምምነት ሒደት ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በፊርማ ሥነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፥ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዛሬው ሥምምነትም ህብረቱ ለፕሪቶሪያው ሥምምነት ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው ብለዋል።

አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ለመተግበር እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን አድንቀዋል፡፡

አያይዘውም የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ህብረቱ ለፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት ትግበራ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፥ ኮሚሽኑ ድጋፉን በአግባቡ ለሚያስፈልጋቸው እንደሚያደርስ ጠቅሰዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.