የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን ከተሳታፊዎች የተገኙ ግኝቶችን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን ከተሳታፊዎች የተገኙ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የባለሙያዎች ቡድን በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የደረሰበትን ሒደት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፤ ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅቱ 13 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ ተመላክቷል፡፡
ቡድኑ ወደ ስራ ከገባ በኋላም በሀገር አቀፍ ደረጃ 80 የሚደርሱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የምክክር እና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በማካሄድ ሕዝባዊ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራ ሰርቶ ማጠናቀቁን ነው የገለጸው፡፡
በነበሩ የምክክር መድረኮችም የፖሊሲው አስፈላጊነት በማህበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት እንደታየበት ተጠቁሟል።
በግብዓት ማሰባሰብ ሒደቱ ከተገኙ ግኝቶች መካከልም ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ሃላፊነት እያለባቸው ሃላፊነታቸውን ሳይወጡ የቀሩና በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሒደት ሊኖር እንደሚገባ ግኝቶች አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በውስን ተሳታፊዎች የተገኙ ግኝቶች ሁሉም አጥፊዎች እንደየተሳትፎ ደረጃቸው ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ያመላከተ ግብዓት ተገኝቷል።
በተጨማሪም የፍርድ ሂደትን ለማከናወን በዚሁ ዙሪያ የሚሰራ ልዩ ፍ/ቤት ሊቋቋም እንደሚገባ ግኝቶች ጠቁመዋል።
እርቅና ምህረት ደግሞ አዲስ በሚቋቋም ሀቅ አፈላላጊ አካል ሊሆን እንደሚገባ ከተሳታፊዎች ግብዓት አመላካች ግኝቶች ተገኝተዋል ተብሏል።
በሽግግር ፍትህ ትግበራ ሂደት ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው፣ የስነ ልቦና እና አዕምሯዊ ቀውስ ያገጠማቸው፣ ከፍተኛ አካል ጉዳትና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ተፈናቃዮች፣ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እና መሰል የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ማካካሻ እንዲያገኙ ማድረግ የተሳታፊዎች ሌሎች ግኝቶች ናቸው።
የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ከየትኛው ጊዜ ጀምሮ የተፈፀሙ ጥሰቶችን ያካትታል የሚለውን በተመለከተ የተለያዩ የጊዜ አማራጮች መቅረባቸው ተነግሯል።
በዚህም ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የተፈፀሙ በደሎችን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው እንዲያካትት በተሳታፊዎችና የባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ተጨምሮበት መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል።
በትግበራ ሂደቱ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚኖራቸው ሚና በግልፅ መወሰን እንደሚገባውም ተመላክቷል።
ከዚህ በፊት የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ በደሎችና ቁርሾዎችን በእውነት፣ በፍትሕና በእርቅ በመሻገር ዘላቂ ሰላምና ፍትህ ለማስገኘት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዝግጅት ላይ መሆኑ የሚታወስ ነው።
ሳሙኤል ወርቃየሁ