ኢትዮጵያውያን ዕዳዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን እናደርጋለን – ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ዕዳዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር አዳዲስ ታሪክ በመጻፍ መጭው ትውልድ ሲዘከረው የሚኖር ደማቅ አሻራዎችን በማሳረፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን እናደርጋለን ሲል ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡
ፓርቲው በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ፥ ታሪክን መስማት ብቻ ሳይሆን ታሪክን በመስራት የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናፀና የመደመር ትውልዶች ነን።
ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ነባርና ገናና ስሟን በማደስ ዘመኑን የዋጀ ከፍታና ሀገራዊ የታላቅነት ምዕራፍ ላይ ለማድረስ ታሪካዊ የሆኑ አሻራዎችን በማስቀመጥ በወጥነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
ፓርቲው ፈተናዎችን ተሻግሮ የኢትዮጵያን የታሪክ ስብራት በማረም ዘላቂነት ባለው መሰረት ወደፊት እንድትራመድ ለማድረግ በትጋት እየሰራ ታላላቅ አስደማሚ ዕምርታዎችን ማስመዝገብ መቻሉንም ነው የገለጸው።
አክሎ እንዳለውም ፥ ብልጽግና ከነበሩብን የታሪክ ዕዳዎች ተላቀን የኢትዮጵያን አኩሪና ነባር ታሪካዊ ዕድሎች በመጠቀም ያሉንን በጎ አጋጣሚና ሁኔታ ያገናዘበ ዘመኑንን የዋጀ ውሳኔና ተግባራትን በመፈጸም የሀገሪቷን ከፍታ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።
ኢትዮጵያውያን ስንተባበር በተለያዩ አጋጣሚዎች ያባከናቸውንና ያጣናቸውን ዕድሎች በማረምና በህብረ ብሔራዊ አንድነት ፀንተን በመቆም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንደምንችል በምንከውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን አመላካች ናቸው ሲልም ባወጣው መረጃ አንስቷል።
ኢትዮጵያ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ትብብርና ልማት በማዞር በፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መርህ መሰረት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲ እየገነባች አፍሪካውያን ችግሮቻችንን በውይይትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የፀና ይሆን ዘንድ በተግባር እየሰራ እንደሚገኝም ነው የጠቆመው።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በወደብና ባህር አጠቃቀም ቀጠናውን በልማት የሚያስተሳሰር አፍሪካዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማዳበር አብሮ ለማደግ የሚያስችል ይሆን ዘንድ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የወደብ አጠቃቀምና ባለቤትነት የፓርቲው የልማት አርበኝነትና የዲፕሎማሲ አቅም ውጤት የሚያሳይ ነው ብሏል በመረጃው።
ኢትዮጵያውያን ዕዳዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር አዳዲስ ታሪክ በመጻፍ መጭው ትውልድ ሲዘከረው የሚኖር ደማቅ አሻራዎችን በማሳረፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን እናደርጋለን ሲልም ገልጿል።
የኢትዮጵያን ሙሉ አቅምና ብልፅግናዋ ሊረጋገጥ የሚችለው ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ አሻራዎችን በማሳረፍ ዘላቂ ሰላምና ሀብትን መፍጠር የሚችል ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው ሲልም ፓርቲው ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ታሪካዊ ስብራቶችን በጥበብ እና በማስተዋል በቆራጥነት እየጠገንን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ዕውን በማድረግ አዳዲስ አኩሪ ታሪኮችን ሰርቶ ለትዉልድ ማሻገር እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘበው።
ኢትዮጵያዊያን ነባር አኩሪ ታሪኮቻችንን ጠብቀን ጉድለቶችን በማረም ለትውልድ የምትመች የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናደረጋለን ሲልም በመረጃው አንስቷል፡፡