በሲዳማ ክልል የበዓል ወቅት የእርድ እንስሳት ዋጋ የተረጋጋ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከገና (ልደት) በዓል ግብይት ጋር ተያይዞ የዕርድ እንስሣት ዋጋ መረጋጋት ማሳየቱን የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከመደበኛ ገበያ ባነሰ ዋጋ ምርቶች የሚሸጡባቸው 46 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መቋቋማቸውን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወጤ ቶሼ ቡቼ ተናግረዋል፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የሲዳማ ኤልቶ ዩኒዬን እንዲሁም በርካታ የግል ነጋዴዎች የተሳተፉበት ከሰኞ እስከ ሰኞ በጊዜያዊነት ገበያ ቦታዎች በሀዋሳና በተለያዪ ከተሞች መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
በጊዜያዊና በመደበኛ ግብይት ማዕከላት÷ ጤፍ፣ ገብስ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ቅቤ፣ አይብ፣ በግ፣ ፍየል እንዲሁም የዕርድ ሰንጋ በሚፈለግ ደረጃ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የስንዴ ዱቄትና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የኢንዱስትሪ ምርቶች በባዛሩ መቅረባቸውን ለለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የበዓል ሰሞን ግብይትም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጤፍና በቆሎ የዋጋ ጭማሬ ሲስተዋል÷ በአንጻሩ የዕርድ እንስሣት (በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮና በእንቁላል) ቅናሽ አሳይተዋል ብለዋል፡፡
ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል የሚሰራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ ምርቶችን ከደላላ ጣልቃ ገብነት ነጻ በማድረግ በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር መፍጠር መቻሉም ነው የጠቆሙት፡፡
በዮሐንስ ደርበው