Fana: At a Speed of Life!

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2ኛ ትውልድ በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መስህቦችን ለማስጎብኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2ኛ ትውልድ የኦሮሞን ባህልና እሴት እንዲሁም የቱሪስት መስህቦች ለማስጎብኘት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የቱሪዝም ገበያ ልማትና ብራንድ ባለሙያ አቶ በረከት ደሴ እንደገለጹት÷ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2ኛ ትውልድ ሀገራቸውን እንዲጎበኙ የቀረበው ጥሪ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ የማነቃቃት ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በኦሮሚያ ክልል የሚኖራቸውን ቆይታ ስኬታማ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ እና የኦሮሞን ባህል እና እሴት እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በ23 የክልሉ ከተሞች የሚገኙ የኮሚሽኑ መዋቅሮች ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ በረከት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞን የአለባበስ ሥርዓት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎች እና ሌሎች እሴቶችን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚዘጋጁም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ኢትዮጵያውያኑን ለማስተናገድ ዝግጅት መጀመራቸውን ጠቁመው÷ በአገልገሎቶች ላይ ቅናሽ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

አቶ በረከት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2ኛ ትውልድ ወደ ሀገራቸው መጥተው የሀገራቸውን ባህል እና እሴት እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ ሃብት በመገንዘብ በቱሪዝም ዘርፍ እና በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.