Fana: At a Speed of Life!

በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ኦዳ ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ለፖሊስ ፈቀደ።

ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ ከዚህ በፊት ለፖሊስ በተሰጠው የ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ የተሰሩ የምርመራ ውጤቶችን ተመልክቷል።

በዚህም መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የ12 ሰው ምስክር ቃል መቀበሉን፣ ለብሄራዊ መረጃ ደህንነት የቴክኒክ ማስረጃ መጠየቁንና ሌሎች ተግባራትን እንዳከናወነ አብራርቷል።

መርማሪ ፖሊስ ቀረኝ ያላቸውን ማለትም ከጳውሎስ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ውጤት ለማቅረብ፣ ከሟች የተወሰደ ንብረትን የማስመለስ ስራ እና ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት ተቋም ቀሪ ማስረጃ ለመሰብሰብ፣ በተጨማሪም ተጠርጣሪው ፍቃድ አውጥቶ የተቀበለውና በተመሳሳይ ተግባር በሌላ ሰው ላይም የመተኮስ ተግባር ፈጽሞበታል ተብሎ የተጠረጠረበት የጦር መሳሪያን መደበቁን የገለጸው ፖሊስ ይህን መሳሪያ አፈላልጎ የማቅረብ ስራ እንደሚቀረው ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።

እንዲሁም ወንጀሉ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ፣ ቀጥተኛ ምስክር የሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችና በልመና ላይ የተሰማሩ ምስክሮች አድራሻ በመቀየራቸው ምክንያት አፈላልጎ ቃላቸውን የመቀበል ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ፤ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን አጠናቅቆ ለማቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ለፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ የተሰራ አዲስ ነገር የለም በማለት የፖሊስን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ በመቃወም ተከራክረዋል።

በተጨማሪም የተጠርጣሪው ጠበቃ ደንበኛቸው ከለሚ ኩራ ፖሊስ ፍቃድ የወሰዱት የጦር መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰው በጦር መሳሪያው የተፈጸመ ወንጀል የለም በማለት ተከራክረዋል።

ፖሊሰ ከጠየቀው የ14 ቀናት ያጠረ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ጅምር የምርመራ መዝገብ እንደመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግ በማመን ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

ተጠርጣሪ ተስፋዬ ሆርዶፋ በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ኤድናሞል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባሉ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል በሚል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.