የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎችን ያካተተ ቡድን የተለያዩ ድጋፎችን በመያዝ በዛሬው እለት ወደ መቀሌ አቅንቷል።
የቡድኑ አባላት በመቀሌ አሉላ ኣባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ቡድኑ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን÷ በዚህም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የትግራይ ክልል ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው ወደ ቀደመው የልማት ስራ ሲመለስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ ሁሉም አካል ለዚህ ተግባር ደጋፊ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ጦርነት በጣም ከባድ ነው ያሉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የክልሉ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቸው የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የትግራይ ህዝብን ለመደገፍ የተለያዩ አልባሳትንና ምግብ ነክ እገዛዎችን ይዘን መጥተናል ያሉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ÷ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመውን ድርቅ ለመከላከል መተጋገዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናስ ቢሮ ሀላፊ ምህረት በየነ (ዶ/ር)÷ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በክልሉ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡