Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ክልከላ በተደረገባቸው መንገዶች ላይ በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልከላ በተደረገባቸው መንገዶች ላይ ሕጉን ጥሰው በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለጸ።

ከሰሞኑ ከቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ፓርላማ ድረስ ያለው መንገድ ለሞተር ሳይክል እና ከ2 ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች መከልከሉ ይታወሳል፡፡

በትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እና በትራፊክ ፖሊሶች ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱንም ነው በባለስልጣኑ የቦሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ብሩክ ዋቅወያ የተናገሩት፡፡

ከዚህ በኋላ ክልከላውን ጥሰው መንገዱን የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች በትራፊክ ሕጉ መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልፀዋል፡፡

መንገዱ በሰዓትና በቀን የተገደበ ሳይሆን 24 ሰዓት ክልክል መሆኑን ጠቅሰው÷በከተማዋ ቋሚ የትራፊክ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ እንደሁኔታው ሊሻሻል ወይም ባለበት ሊቀጥል እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

አማራጭ መንገድ የሌላቸው የኮንስትራክሽን ስራ የሚሰሩ እና የነዳጅ ማደያ ተሽከርካሪዎችም ጥያቄ ሲያቀርቡ እና ቦታው ታይቶ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ እንዲንቀሳቀሱ ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሚችል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.