Fana: At a Speed of Life!

ርዕሳነ-መሥተዳድሮች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ-መሥተዳድሮች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው በመልዕክታቸው÷ የጥምቀት በዓል ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ አንድነትንና ሌሎች መልካም የማኅበራዊ መስተጋብሮቻችና እሴቶቻችን ጎልተው የሚታዩበት ነው ብለዋል።

በዓሉን ለማክበር የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ወቅቱ በየጊዜው ለሚያጋጥሙ ፈተናዎች እጅ ከመስጠት ይልቅ አንድነት በማጠናከር የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል የተለየ እድል የሚገኝበት መሆኑን አመላክተዋል።

የክልሉን ጸጋዎች ለውጤት ማብቃት፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት፣ የቱሪዝም ሀብቶችን ማልማትና ማስተዋወቅ፣ የስራ እድል መፍጠር፣ ግብርናውን ማዘመን እና ሌሎች አያሌ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተሻለ አቅም ለመፈጸም ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሐረሪ ክልል መንግስት ባስተላለፈው መልዕክት÷ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም በተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባሕሉን በመተግበር እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንም ተመኝቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት÷ አንድነትን በማጠናከር፣ የዕርቅና የይቅርታ ድልድይ በመገንባት የሀገራችንን ነጻነት ለማስከበር በቁርጠኝነት መሥራት አለብን ብለዋል።

የተከማቹ ችግሮች ተፈትተው መጪው ትውልድ ሰላማዊና ነጻ ሀገር እንደሚወርስ ገልጸው÷ ከሕዝብ ጋር በመሆን እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ትላልቅ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኅብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ያለው ለሌለው የመደገፍና የመርዳት ባሕሉን በማጠናከር ሊሆን ይባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በዜጎቿ ጥረት እየተሻገረች ለዚህ በቅታለች ያሉት አቶ ኡሞድ÷ በክልሉ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የከተራ እና ጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ÷በዓሉን ስናከበር ሰላምን በማጽናት፣ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

ለጋራ ሰላማችን መጽናት ሁሉም አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባልም ነው ያለው።

በዓሉን ስናከብር በወንድማማችነት ስሜት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ፣ በመፈቃቀድ በመተሳሰብና በመደጋገፍ በሰላም፣ በፍቅርና በደስታ እንዲሆንም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ÷የጥምቀት በዓል የትህትና ተምሳሌት ነው ፤ በዚህም እርስ በርስ መከባበር፣ መተሳሰብና ይቅር መባባል የበለጠ እንዲጎለብት ለማድረግ ከበዓሉ የተማርነውን ትህትና በተግባር መግለጥ  ይጠበቃል ብለዋል፡፡

 

የጥምቀት በዓል አከባበር በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን በአግባቡ መጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር  የሁሉም ድርሻ  ነው ብለዋል።

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.