በከተሞች እየጨመረ የመጣውን ህዝብ ሊሸከም የሚችል የቤት አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ብዛት ሊሸከም የሚችል የቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማሳሰቢያ ተሰጠ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ሲያካሂድ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
በስብሰባው የከተማ እና መሰረተ ልማት ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ÷ በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን፣ የአሰራር ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አለመኖር በመደለያና ባልተገባ የጥቅም ትስስር አገልግሎት መስጠት፣ ህገወጥነትና ብልሹ አሰራር መስፋፋት በመኖሩ ተገልጋዩ ቅሬታ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
በመሆኑም የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን፣ ብልሹ አሰራርን ለማጥፋት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ምን እየሰራ እንደሆነ በቋሚ ኮሚቴው ተጠይቋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት÷ በከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የከተሞች ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎትን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
500 ሚሊየን ዶላር ለሁለተኛ ዙር የከተሞች ተቋማዊ እና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም፣ ለአዲሱ የተቀናጀ መሬት ማኔጅመንት ፕሮግራም 100 ሚሊየን ዶላር፣ ለገጠር ትስስር ተደራሽነት ፕሮግራም 300 ሚሊየን ዶላር በጥቅሉ ከ900 ሚሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት መፈጸሙን ጠቅሰዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ምህንድስና አቅም ግንባታን እውን ለማረግ የልማት ጥረቶችን በማቀናጀት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የኮንስትራክሽን ምህንድስናና ማኔጅመንት የልህቀት ማእከል ተቋም ለማቋቋም የዲዛይን፣ የአፈር ምርመራና የቅየሳ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የሕግ ማዕቀፎች አለመጽደቅ፣ የሲሚኒቶ አቅርቦት ውስንነት፣ ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉና በከፊል መቆማቸው እንዲሁም የስራ ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶች የመፈጸም አቅም ማነስና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት