የባህል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍተቶችን በመሙላት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህል ፍርድ ቤቶች የፍትህ እና የዳኝነት አገልግሎት ክፍተቶችን በመሙላት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የክልሉ የባህል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጫ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ የባህል ፍርድ ቤቶች የማኅበረሰቡን እሴትና ባህል ባከበረ፣ ችግርን በሚፈታ እና ቂምና በቀልን በሚሽር መንገድ ፍርድ ይሰጣሉ።
በመሆኑም ለባህል ፍርድ ቤቶች የተሰጠው እውቅና ትልቅ ዋጋ ያለው ነው ብለዋል።
የባህል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና የመደበኛ የዳኝነት ተቋማት ተደራሽነት ላይ ያለውን ጉድለት የሚሞሉ መሆኑን ገልጸው፤ የፍትህና ዳኝነት ክፍተት በመሙላት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ ባህላዊ አለመግባባቶችን መፍቻ ዘዴዎች ግጭትን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የሰዎችን ዘላቂ ግንኙነት በማስቀጠል ለዘመናት አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት በክልሉ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው ለዘመናት ያገለገሉ ባህላዊ አለመግባባቶችን የመፍቻ ሥርዓቶች ሲተገብሩ የነበሩ 15 ባህላዊ ተቋማት የባህል ፍርድ ቤት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ ዕውቅና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የባህል ፍርድ ቤቶች ተአማኒና ገለልተኛ ሆነው ሰብአዊ መብቶችን በመጠበቅ እንደሚሠሩ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ዛሬ ዕውቅና የተሰጣቸው የባህል ፍርድ ቤቶች በ4 ሺ ቀበሌዎች ላይ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የባህል ፍርድ ቤቶች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት አማራጭ ፍርድ ቤት በመሆን የዳኝነት እና የፍትህ ሥርዓቱን ማገዝ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ለዚህም የአሠራር ሥርዓቶችን፣ መመሪያዎችን፣ ተቋማዊ ድጋፍ መስጠት የሚያስችሉ አደረጃጀቶች ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የባህል ፍርድ ቤትነት ዕውቅና የተሰጣቸው ሽምግልና፣ አበጋር፣ ረከቦት፣ ዱለት፣ አማሬ ቁና፣ አውሳይድ ፣ ጎራው አባ አሊ፣ ስምንቱ ማይ ቤት፣ ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ክፍሎ፣ ሰንዬሰገድ፣ አባሀጋ፣ ዙፋን ዋልዋጅ እና ሰባቱ ከዘራ ናቸው።
በደሳለኝ ቢራራ