አራት ግለሰቦችን ያለ አግባብ በማሰር ገንዘብ እንዲከፍሉት አስገድዷል የተባለ የፖሊስ አባል በእስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አራት ግለሰቦችን ያለ አግባብ በማሰር ገንዘብ እንዲከፍሉት አስገድዷል የተባለ የፖሊስ አባል በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የዞኑ ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ ረዳት ሳጅን ጌታቸው መኮንን በቅጽል ስሙ (ተረፈ) ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 423 የሙስና አዋጁን 881/2007 አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላለፏል በማለት ተደራራቢ ክስ አቅርቦበታል።
ተከሳሹ ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በወረ ጃርሶ ወረዳ የፖሊስ አባል ሆኖ ሲሰራ በተለያየ ጊዜ አራት ግለሰቦችን ያለ አግባብ በማሰር ከ5 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መጠን ”ካልከፈላችሁ ከእስር አትፈቱም ” በማለት በማስፈራራት ከግለሰቦቹ 180 ሺህ ብር መቀበሉን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።
ተከሳሹ የቀረበበት ክስ ዝርዝር በችሎት ከደረሰው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የግል ተበዳዮቹን ጨምሮ የተለያዩ የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦበታል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻሉ ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየትና የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት መርምሮ ተከሳሹንም ሆነ ሌሎችን ያስተምራል በሚል በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ