Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ከእነ ክብሯ ለማሸጋገር የዓድዋ ድል መታሰቢያ አስፈላጊ ነው አሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከእነ ክብሯና ነጻነቷ ለልጆቻችን ማሸጋገር እንዲቻል የዓድዋ ድል መታሰቢያ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ የተገነባውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ መርቀዋል፡፡

በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግርም ይህንን አስደማሚ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሌሎች የጥቁር ሕዝቦች ሀገራት ሊሠሩት ቢችሉም፤ የምኒልክ ልጅ፣ የባልቻ ልጅ፣ የገበየሁ ልጅ፣ የአሉላ አባ ነጋ ልጅ መሆን ግን አይችሉም ብለዋል፡፡

የሰው ልጅ የሕይወት ጉዞ በዕድልና በትግል የተሞላ ነው፤ ዕድል ከሌለ ትግል ብቻውን ስኬት አያመጣም፤ የዓድዋ ድልም ኢትዮጵያውያን የታደልነው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሙሉ ዕድለኞች ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ዕድለኞች ያደረገን ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆናችን ነው ብለዋል፡፡

የድል መታሰቢያውን ሰርተንና ጥረን ያሳካነው ነው፤ ከ128 ዓመታት በኋላ ተገንብቶ ለትውልድ ማለፍ በሚችልበት መልኩ ኢትዮጵያን መስሎ ተሠርቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ነገር ሲሰራ ፈተና እንዳለበት አመላክተው ኢትዮጵያ ከዓድዋ እስከዛሬ የፈተናዎቿ ምንጮች ባዳዎችና ባንዳዎች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

አባቶች በምን መደጋገፍ፣ በምን መተባበር፣ በምን መከራከርና መነጋገር እንዳለባቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ፈተናዎችን ከአባቶች መማር እንደሚያስፍልግም ጠቁመዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያን ማርከስ ማለት የአባቶቻችንን አጥንት እና ደም ማርከስ ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

እምቢ ማለት ለወራሪና ለድህነት፣ ለልመና እንዲሁም ለውጫዊ እሳቤ መሆኑን በመግለጽ÷ይህንን ነጻነት እና ክብር የወረሰ ኢትዮጵያዊ ዛሬም የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚተጋ መሆን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.