Fana: At a Speed of Life!

ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ 5 ሺህ 426 የክላሽንኮቭ ጥይት ተያዘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 04፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ 5 ሺህ 426 ሕገ-ወጥ የክላሽንኮቭ ጥይት ወልድያ ፍተሻ ጣቢያ ላይ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከአሸባሪዎች ተልዕኮ ተቀብሎ በመሃል ሀገር በአዲስ አበባ እና በአካባቢው የሽብር ተግባር ለመፈፀም መነሻውን ቆቦ ከተማ ያደረገው ተጠርጣሪ በሃይሩፍ መኪና ላይ ጥይት ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በማጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው በወልድያ ከተማ የተያዘው፡፡

ተጠርጣሪው የወልድያ ፍተሻ ጣቢያን ለማለፍ ሲሞክር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተሽከርካሪው ላይ ባደረገው ጥብቅ ፍተሻ 5 ሺህ 426 ሕገ-ወጥ የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ጥይት መያዙን አስታውቋል።

ጥይቱን አስጭኖ ሲያጓጉዝ የነበረው ተጠርጣሪ እና የመኪናው ሾፌርም ከነ-ኤግዚብቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

አሸባሪዎች በተደጋጋሚ በመሀል ሀገር በአዲስ አበባና አካባቢው የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚወጥኑት የሽብር ዓለማ በየጊዜው በፀጥታና ደኅንነት አካላት ፈጣን ሕጋዊ እርምጃ እየከሸፈ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ፖሊስ እነዚህ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በሽብር ቡድኑ እጅ ቢገቡ ኖሮ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ይችሉ እንደነበር ነው ያስገነዘበው፡

፡ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

ኀብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.