Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባዔ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 15ኛው ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባዔ በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቀጣዩ ዓመት ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባዔን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡

በዚህ መሰረትም የዓለም የምልክት ቋንቋ ጉባዔ በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ ከጥር 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መስማት ከተሳናቸው ማህበርና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጉባዔውን ለማካሄድ ዝግጅት መጀመሩን ኤርጎጌ (ዶ/ር) አንስተዋል።

ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉና የሀገራትን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ጉባዔው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን በመግለጽ የተቋማቸው ምሁራን ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በጉባዔው ከተለያዩ የዓለም ሀገራትና ተቋማት የተወጣጡ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.