ነጠላ ትርክቶችን በመተው የጋራ የሚያደርጉ ገዢ ትርክቶችን ለማጽናት መስራት ይገባል – አቶ ሙስጠፌ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚያለያዩ ነጠላ ትርክቶች በመተው የጋራ የሚያደርጉ ገዢ ትርክቶችን ለማጽናት በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ገለጹ፡፡
“ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ” በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የቦንጋ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በዞኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሆነው የሰነበቱ ምላሽ እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል ።
ከለውጡ ማግስት በዞኑ እየተስተዋሉ ያሉ ጅምር የልማት ሥራዎች በዘላቂነት ለፍጻሜ እንዲበቁ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽ አለመሆን፣ የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚዬም ወደ ሥራ አለመግባት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ዜጎች በነጻነት ተዘዋውረው እንዳይሰሩ የሚገታ ተግባር በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በሹመት፣ በቅጥርና መሰል ጉዳዮች አሁንም በዘመድ አዝማድ የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮች መኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈተሽ ይገባልም ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ÷ የሚነሱ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
ከለውጡ ማግስት በርካታ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መምጣታቸውንና ወደ ፊትም የሚመለሱ ጉዳዮች በመመካከር እና በመነጋገር እልባት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የሚያለያዩንና የሚያናቁሩንን ነጠላ ትርክቶች በመተው የጋራ የሚያደርጉንና ገዢ የሆኑ ትርክቶችን በማጽናት ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
የተሳለጠ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከህዝቡ የተነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መሠረታዊ እውነታዎች በመሆናቸው ለችግሮቹ መፍትሔ በጋራ ጥረት እናደርጋለን ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።