ፖሊስ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ሦስት አዘዋዋሪዎችን ጨምሮ 117 ከሀገር ሊወጡ የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ተታልለው በሶማሌ ክልል በኩል ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ቶጎ ውጫሌ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡
የአብዛኞቹ ዕድሜም ከ15 ዓመት አለመብለጡን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ የሰው ልጅን ማዘዋወር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ተገንዝቦ መሰል ድርጊት ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡