በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከሊኖቮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከሊኖቮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በትበብር መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ሲቲ እና መሰል የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንትን የሚያግዝ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በመንደፍ እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከካምፓኒው የመጡት የሥራ ሃላፊ ማርቲን ያላ በበኩላቸው÷ ሊኖቮ የቴክኖሎጂ ተቋም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የመስራት ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል፡፡
ተቋማቸው አነስተኛ የቢዝነስ ድርጅት ሆኖ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያለውን የሥራ ልምድ ያቀረቡ ሲሆን÷በኢትዮጵያ በዘርፉ ለመስራትና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማገዝም ቃል ገብተዋል፡፡