Fana: At a Speed of Life!

1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ሥራ መጀመራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ሥራ መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 የሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግመገማ እየተካሄደ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል÷ የግምገማው ሂደት ትኩረት ካደረገባቸው ኢኮኖሚያዊ መስኮች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ አፈጻጸም መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በተለያዩ ችግርች ደካማ እንደነበር ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በስፋት ወደ ምረት እንዲገቡ መደረጉን አስታውሰዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተወሰዱ እርምጃዎች የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 56 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።

ከፋይናንስ፣ ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከሰው ኃይል፣ ከገበያ ትስስር፣ ከኤሌክትሪክና መሰል መሰረተ ልማቶች ማሟላት አኳያ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት ውጤቱ የማምረት እቅም ማደጉን ተናግረዋል።

የፍጆታ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ለወጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን ገቢ ምርት መተካት ላይ የተሰጠው ትኩረት በግምግማው በአዎንታዊ አፈጻጸም መነሳቱን ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በተኪ ምርት 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 994 ሚሊየን ዶላር መሳካቱን ጠቅሰው÷ አፈጻጸሙም 93 በመቶ መሆኑን አንስተዋል።

በግማሽ ዓመቱ 67 የውጭ ባለሀብቶችን በኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 127 ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

ከሀገር ውስጥ ደግሞ 2 ሺህ 300 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ታቅዶ 1 ሺህ 490 ያህል ወደ ዘርፉ ተሰማርተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢንቨስትመንት ከማሰማራት ባለፈ ባለፉት ስድስት ወራት የውጭና ሀገር በቀል ኢንዱስትርዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በተሰራው ስራ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለ142 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ121 ሺህ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ከወጪ ንግድ አኳያ ዘርፉ ያለው ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲያድግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.